አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡
ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አቅጣጫ ተቀምጦ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ተማሪዎች ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የዘንሮውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ቢሮው ከትምህርት ሚኒስቴርና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እንዲሁም ከክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በትበብር የፈተና ጣቢያዎችን እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፈተናውን በበይነ መረብ ብቻ ለመስጠትም በፈተና ጣቢያዎቹ የኮምፒውተር፣ ኔትዎርክ፣ ኤሌክትሪክና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ተማሪዎች የሞዴል ፈተናዎችን በመውሰድና በመለማመድ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናውን በበይነ መረብ ብቻ መውስድ የሚያስችል ክህሎት እንዲኖራቸው ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ተማሪዎች ስነ ልቦናዊ ዝግጅትን ጨምሮ በተሟላ መልኩ ለፈተናው በሚገባ ዝግጁ እንዲሆኑ መምህራን፣ ወላጆች እና ሌሎች የትምህርቱ ማህበረሰብ አባላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገቀር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ከ190 ሺህ በላይ መሆኑን ካሳሁን ገላና (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

