አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞችን መረጃ ማዘመን የሚያስችል ፕሮጀክት የሙከራ ትግበራ አስጀመረ፡፡
ባለስልጣኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ÷ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው በተቋሙ ያለው የመረጃ አያያዝ ስርዓት አለመዘመን አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ጠቅሰው÷ አሁን ላይ በዘመናዊ መልክ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት መተግበሩን አስረድተዋል።
መረጃ የሚሰበሰበው አሁን ካሉ የባለስልጣኑ ደንበኞች እና ወደፊት ደንበኛ ሊሆኑ ከሚችሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የመዲናዋ ነዋሪዎች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የ600 ሺህ ደንበኞችን አርካይቭ መልሶ የማደራጀትና በተገኘው መረጃ መሰረት ውል እንዲያድሱ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
የቆጠራና የመረጃ መሰብሰብ ስራው በባለስልጣኑ 10 ቅርንጫፎች እንደሚተገበርና በዛሬው ዕለት በመገናኛ ቅርንጫፍ በሙከራ ደረጃ ትግበራው መጀመሩን ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታት ደግሞ በሌሎች ቅርንጫፎች በሦስት ምዕራፍ እንደሚተገበር አንስተው÷ ትግበራው ሲጠናቀቅ ደንበኞች አዲስ የውሃ ቆጣሪ ማስገባትን ጨምሮ ባሉበት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለውን አገልግሎት በኦንላይን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የውሃ ብክነት ያለባቸው ቦታዎችን በመጠቆም ለመቀነስ፣ የነባር ደንበኞች ውል በጊዜው እንዲታደስ በማድረግና ለአዳዲስ ደንበኞች አገልግሎቱን በፍጥነት በማዳረስ ገቢው እንዲጨምር ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ደንበኞች የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የሚጠይቋቸውን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
አሁን ላይ በመዲናዋ ከ700 ሺህ በላይ የውሃ ደንበኞች፣ ከ300 ሺህ በላይ የፍሳሽ ቅጥያ ተጠቃሚዎች መኖራቸው እንዲሁም በቀጣይ ከኮንዶሚኒየም ውጭ ነባር ይዞታ ላይ ያሉ ከ600 ሺህ በላይ የውሃ ተጠቃሚዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
በመሳፍንት እያዩ

