አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ወደ 16ቱ ለመግባት አራት የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
በመልስ ጨዋታዎች ቤነፊካን በመጀመሪያው ዙር 1 ለ 0 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ በቤርናቦው ምሽት 5 ሰዓት ላይ የመልሱን ጨዋታ ያደርጋል።
በተመሳሳይ ሰዓት ሞናኮን ከሜዳው ውጪ 3 ለ 2 ያሸነፈው ፒኤስጂ የመልሱን ጨዋታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ሲያካሂድ፤ በጋላታሳራይ የ5 ለ 2 ሽንፈት የገጠመው ጁቬንቱስ ውጤቱን ለመቀየር በሜዳው ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።
ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በዶርትሙንድ የ2 ለ 0 ሽንፈት የገጠመው አታላንታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ወደ 16 ውስጥ ለመቀላቀል ይጫወታል።
ትናንት ምሽት በተደረጉ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች 4 ቡድኖች ወደ 16ቱ መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም ባየር ሊቨርኩሰን ኦሎምፒያኮስን 2 ለ 0፣ ቦዶ ግሊሚት ኢንተር ሚላንን 5 ለ 2፣ ኒውካስል ዩናይትድ ካራባግን 9 ለ 3 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ክለብ ብሩዥን 7 ለ 4 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ 16ቱ ተቀላቅለዋል።

