አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎርፍን በአግባቡ በማስተዳደር የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና ለልማት ማዋል ይገባል አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
በስምጥ ሸለቆና በኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ላይ ያተኮረ የጎርፍ ተጋላጭነት ሁኔታና የመከላከል ስራን በተመለከተ በተዘጋጀው ጥናት ላይ በሀዋሳ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ በአዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆና ኦሞ ጊቤ ተፋሰሶችን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚታዩ የጎርፍ አደጋዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በዓመት በቀጥታ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎችን በጎርፍ አደጋ እንደሚጎዱ ጠቅሰው÷ ለዚህም በጊዜያዊነትና ዘላቂነት የመከላከል ስራዎች በመንግሥት፣ በልማት አጋሮች እና በዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ትብብር መፍትሄ የመስጠት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሦስቱም ተፋሰሶች በዘላቂነት የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ጥናት ተደርጎ ወደ ትግበራው ለመግባት የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ደርሷልም ነው ያሉት።
በ2017/2018 በሦስቱም ተፋሰሶች ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው÷ ለዚህ መፍትሄ አንዲሆን የጊዜያዊና መካከለኛ ጊዜ ስራ በ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር 256 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መከላከያ ዳይክ ስራ በመሰራቱ 229 ሺህ በላይ ዜጎች ከመፈናቀል መትረፋቸውን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከጎርፍ መከላከያ ግንባታ በተጨማሪ የሚቲዎሮሎጂ መረጃን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ከ1 ሚሊየን የሚበልጡ ዜጎችን ከጎርፍ አደጋ መታደግ መቻሉም ተገልጿል።
በጌታቸው ሙለታ

