Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕክምና ኦክስጅን አቅርቦትን ለማሻሻል…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻዎች ቁጥር 85 ደርሷል አለ የጤና ሚኒስቴር፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በሕክምና ኦክስጅን አቅርቦት ዙሪያ ከክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መክረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታዋ በዚህ ወቅት÷ የኦክስጅን ሥነ ምሕዳርን ለማጠናከር ሚኒስቴሩ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሶስት ብቻ የነበሩትን የኦክስጅን ማምረቻዎች ዛሬ ላይ 85 ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

የሕክምና ኦክስጅን አቅርቦትን ለማሻሻልና ያሉንን ውስን ሃብቶች በአግባቡ ለመጠቀም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሜዲካል ኦክስጅን ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት ሶላርን እንደ አማራጭ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢሉባቡር ቡኖ በበኩላቸው÷ በሕክምና ኦክስጅን ማሽን ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ተሞክሮ የማጋራትና ሥልጠና የመስጠት ሥራ እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአንድ ሆስፒታል የኦክስጅን ማዕከል መኖሩ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ መገለጹንም ዶ/ር ኢሉባቡር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version