የውክልና ዴሞክራሲ የሚተገበረው የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን ይዘው ከቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መራጩ ህዝብ ይበጀኛል የሚለውን ሲመርጥና የአሸናፊው ፓርቲ (ፓርቲዎች) ተወካይ ወይም ተወካዮች ደግሞ የሕግ አውጪውንና የሕግ እስፈጻሚውን ለተመረጡበት የምርጫ ዘመን ተረክበው ሲያስተዳድሩ ነው፡፡
ይህ የሕዝብ ውክልና በሕግ በተቀመጠው መሠረት በየጊዜው በተወሰነለት የጊዜ ሰሌዳ መታደስ ይኖርበታል፡፡
ይህም ማለት በኢትዮጵያ ወስጥ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት ተወካዮች ምርጫ በየአምስት አመቱ የሚካሄድ ስለሆነ የህዝብ ውክልና የሚታደሰው በየአምስት አመቱ ነው ማለት ነው፡፡
ይህ የሚያሳየው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተግበር ምርጫ የማይተካ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው፡፡
የዴሞክራሲ ዋና መገለጫ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካኝነት እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ስርዓት ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ የሚመረጡት ለዚሁ ተብለው በሚዘጋጁ ምርጫዎች አማካኝነት ነው፡፡
ለዚህም ነው ዴሞክራሲን ያለ ምርጫ ማሰብ አይቻልም የሚባለው፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት፦
ሀ) በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በህዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፣
ለ) እድሜው 18 አመት ሲሞላ በሕግ መሰረት የመምረጥ፣
ሐ) በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ፤ ምርጫው ሁሉን አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡
እርስዎ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተዘጋጅተዋል?
ድምጽዎ ዋጋ አላት!

