Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓትና የሚካሄዱ የምርጫ አይነቶች….

በኢትዮጵያ አምስት የምርጫ አይነቶች ይካሄዳሉ፡፡ እነሱም፡- ጠቅላላ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ማሟያ ምርጫ፣ ድጋሚ ምርጫ እና ህዝበ ውሳኔ ናቸው፡፡

⚙️ጠቅላላ ምርጫ ፡- ይህ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡ ጠቅላላ ምርጫ በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እና ጉዳዩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላል፡፡

⚙️የአካባቢ ምርጫ፡- በህግ በተደነገገው መሰረት በየደረጃው በሚገኙ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡ በአካባቢ ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል ምን ያህል ተወካዮች እንደሚመረጡ እንደየምርጫው ዓይነትና ለየምክርቤቱ የሚመረጡትን አባላት መሠረት በማድረግ በየክልሎቹ ህግ ይወሰናል፡፡ የአካባቢ ምርጫ ምንም እንኳን ዝቅተኛ መስፈርቶችን በተመለከተ የፌዴራሉ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ሕግ ሊያወጣ እንደሚችልና የክልል ሕጎች የሕገ መንግስቱንና የአዋጅ ቁ.1162/2011ን መስፈርቶች ያሟሉ መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡

⚙️የማሟያ ምርጫ፡-የሚካሄደው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በተለያየ ምክንያት የተጓደሉባቸው አባላት እንዲሟሉላቸው ለቦርዱ ጥያቄ ሲያቀርቡ ወይም በህጉ መሠረት የቀረበ የተወካይ ይነሳልን ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ሊያልቅ ስድስት ወራት የቀረው ከሆነ የማሟያ ምርጫ አይካሄድም፡፡

⚙️ድጋሚ ምርጫ፡- ከሚካሄድባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በምርጫው ሂደት በተከሰተ የሕግ መጣስ ወይም ማጭበርበር ወይም የሰላም መደፍረስ ምክንያት የምርጫው ውጤት ተዛብቷል ብሎ ቦርዱ ሲወስን ነው፡፡ ሌላው ምክንያት እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በማግኘታቸው ምክንያት አሸናፊውን መለየት አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ድጋሚ ምርጫ ሲካሄድ ሌላ አዲስ የመራጮች ምዝገባ ሳያስፈልግ በምርጫ ክልሉ ወይም ችግሩ የተከሰተባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ተመዝግበው በነበሩ መራጮች ይካሄዳል፡፡ በተጨማሪም ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወሰን አዲስ የእጩዎች ምዝገባ ሳያስፈልግ ቀድሞ በተመዘገቡ እጩዎች መካከል ብቻ እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡ በድጋሚ ምርጫ ሂደት የምርጫ ቅስቀሳ አይደረግም፡፡

⚙️ሕዝበ ውሳኔ ፡- በህገ መንግስቱ መሰረት አግባብ ባለው አካል ሲወሰን የህዝብን ፍላጎት ለመለካት ወይም ለመወሰን ድምጽ የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ የወሰነው አካል በሚሰጠው መመሪያ መሰረት የምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ ያስፈለገበትን ጉዳይ ለመለየት በሚያስችለው መልኩ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን በማደራጀት ህዝበ ውሳኔውን ያከናውናል፡፡

Exit mobile version