አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በክልሉ ባለፉት ዓመታት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ውጤት አምጥተዋል አሉ።
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከአልሚ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፎረም በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የተፈጠረውን ምቹ መደላድል በመጠቀም የኢኮኖሚ አቅምን ይበልጥ ለማሳደግ መስራት ይገባል፡፡
የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ ተዋናይ መሆን እንዳለበት አስገንዝበው፤ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባለሃብቱን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ በተሰራው ስራ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ እና የመሬት አቅርቦት ላይ የተሻለ ስራ በመሰራቱ የክልሉ የኢንቨስመንት ፍሰት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ባለሃብቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ጉልህ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በክልሉ የተሰማሩ ከ1 ሺህ በላይ ባለሀብቶች ኢኮኖሚውን እየደገፉ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የፋይናንስ እና የመሬት አቅርቦትን ማጠናከርን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመተግበር ዘርፉን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማጠናከር እና ሌሎች ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን መፍታት ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚተገበሩም ገልጸዋል።
በቅድስት በርታ

