Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቴምር ፕሮፐርቲስ የዐብይ እና ረመዳን ጾምን አስመልክቶ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቴምር ፕሮፐርቲስ የዐብይ እና ረመዳን ጾምን አስመልክቶ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርቷል።

በሪል እስቴት ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘው ቴምር ፕሮፐርቲስ በቡልጋሪያ አካባቢ አዲስ ባስጀመረው ሳይት አካባቢ ለሚኖሩ 70 አቅመ ደካማ ዜጎች ነው በዛሬው ዕለት ማዕድ ያጋራው።

የቴምር ፕሮፐርቲስ የኢንቨንትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ኡስማን መሐመድ በዚህ ወቅት ፥ ተቋሙ በአዲስ አበባ የመኖሪያ እና የንግድ ሕንጻዎችን በመገንባት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ከመመለስ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት በማደስ፣ ማዕድ በማጋራትና በተለያዩ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያሳየ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ተቋሙ በመጀመሪያ ቤት ለገዙና በእጣ መኪና ለደረሳቸው ሁለት የተቋሙ ደንበኞች ሁለት ዘመናዊ የቢዋይዲ መኪኖችን ቁልፍ አስረክቧል።

ከ10 በላይ አፓርታማዎችን ሰርቶ ለደንበኞች ያስረከበው ቴምር ፕሮፐርቲስ በ28 ሳይቶች ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝና በዚህ ዓመት የሳይቶቹን ቁጥር 100 ለማድረስ ማቀዱንም አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version