ዋ!… ያቺ አድዋ
ዋ!…
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ…
ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብጽዕና
በመሥዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደገና…
ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰዉብሽ ለት፤
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያነት ምስክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ በትንሣኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው-እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው-በለው-በለው-በለው!
ዋ!… ዓድዋ…
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው፣ በለው- በለው!
ዋ! … ዓድዋ …
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመሥዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሡ እደገና፡፡
… ዋ! … ያቺ ዓድዋ
ዓድዋ ሩቅዋ
የዐለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ…
ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን

