Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከወዲሁ የሚጠበቀው የሪያል ማድሪድ እና ማንቼስተር ሲቲ ፍልሚያ …

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሪያል ማድሪድ እና ማንቼስተር ሲቲ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ በተደጋጋሚ እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ ድልድል ትናንት በስዊዘርላንድ ኒዮን ይፋ ሲደረግ የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ከእንግሊዙ ክለብ ማንቼስተር ሲቲ ተገናኝተዋል፡፡

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ድልድል ላይ የሁለቱ ቡድኖች መገናኘት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል፡፡

የ15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ባለክብሩ ሪያል ማድሪድ እና የአንድ ጊዜ የመድረኩ አሸናፊ ማንቼስተር ሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ ብቻ በቀጣይ የሚያደርጉትን ጨዋታ ሳይጨምር በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ 11 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡

ሪያል ማድሪድ በዚህ የውድድር ዓመት 16ቱን የተቀላቀለው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርጎ ሲሆን ማንቼስተር ሲቲ በበኩሉ በቀጥታ 16ቱን መቀላቀሉ አይዘነጋም፡፡

ውድድሩ በአዲስ አቀራረብ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ሪያል ማድሪድ የዘንድሮውን ጨምሮ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ዓመታት 16ቱን ለመቀላቀል የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን ለማድረግ መገደዱ ይታወቃል፡፡

በ2024/25 የውድድር ዓመት ከውድድሩ በጊዜ የተሰናበቱት ሁለቱ ቡድኖች አሁንም ከሁለት አንዳቸው በጊዜ ለመሰናበት የሚገደዱ ይሆናል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት በሊግ ቅርጽ በተደረጉ ጨዋታዎች በመድረኩ 6ኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው ማንቼስተር ሲቲ ማሸነፉ ይታወቃል፡፡

የማንቼስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በአንድ ወቅት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሸነፍ ሪያል ማድሪድን ማለፍ ግድ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ይደረጋሉ፡፡

በዚህም የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ በሳንቲያጎ ቤርናባው ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ በኢትሀድ የሚደረግ ይሆናል፡፡

የአምና የመድረኩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው በሻምፒየንስ ሊጉ የሚጠበቅ መርሐ ግብር ሲሆን፤ ቡድኖቹ በ2025 በዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ተገናኝተው ቼልሲ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እስካሁን ድረስ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ያሸነፈው አርሰናል ከባየር ሊቨርኩሰን ተደልድሏል፡፡

አርሰናል እስከ ፍፃሜው ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ፒኤስጂ፣ ሊቨርፑል፣ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ባየር ሙኒክ የመሳሳሉ ክለቦችን አያገኝም፡፡

አትሌቲኮ ማድሪድ ከቶተንሀም፣ አታላንታ ከባየርን ሙኒክ፣ ጋላታሳራይ ከሊቨርፑል፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከቦዶ ግሊምት እንዲሁም ባርሴሎና ከኒውካስል ዩናይትድ ሌሎች የ16ቱ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version