አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 130ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በመከላከያ ሰራዊት ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል።
የዕዙ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሙላት ጀልዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በልጆቿ ደም የተጎናጸፈች ድል ነው።
የአሁኑ ትውልድ የጀመረውን ሀገራዊ ግንባታ በማጠናከር ዳግማዊ ዓድዋን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በግፍ ያጣችውን የባሕር በር መልሶ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አቅጣጫ ለማዳከም፣ ለመጉዳት እና እድገቷን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላት ላይ ከአባቶቻችን የወረስነውን ጀብድ በመፈፀም የሀገራችን ጥቅም በማስጠበቅ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለትውልድ እንድትተላለፍ የዳሎል ዕዝ ቁርጠኛ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመርሐ ግብሩ ዓድዋን የሚዘክሩ የተለያዩ ዝግጅቶች ተካሂደዋል።
በተስፋሁን ከበደ

