የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት ያሏቸውን ተጨማሪ መብቶች በአንቀጽ 38 በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
በዚሁ መሰረት የመጀመርያውና ዋነኛው መብት የመምረጥና የመመረጥ መብትን አፈጻጸም በተመለከተ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት አይደረግበትም የሚለው ነው፡፡
ይህ መብት አንድ ኢትዮጵያዊ በማናቸውም የአገሪቱ ክፍሎች በተዘረዘሩት የመድሎ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተረጋገጠው የምመረጥና የመመረጥ መብት አንድ መራጭ የሚመርጠውን ፓርቲ ወይም እጩ በሚስጥር የመምረጥ መብት ያለው መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ይህ መብት በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ (እና በመንግስት) ላይ በተጓዳኝነት መራጩ ድምጽ በሚስጥር ለመስጠት የሚያስችለውን አካባቢያዊና ቴክኒካዊ ሁኔታ የማሟላት ግዴታ ይጥላል፡፡
ከመምረጥ መመረጥ ባሻገር….
በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ዜጎች በመራጭነት እና በተመራጭነት ከመሳተፍ በተጨማሪ ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው ብዙ የኃላፊነት መድረኮች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በምርጫ ታዛቢነት መሳተፍ እና በምርጫ አስፈጻሚነት መሳተፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

