Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ትርክት ቀያሪው የዓድዋ ድል

በ1888 ዓ.ም የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት የጣሊያን መንግሥት ለውጥን እና አውሮፓውያን ለአፍሪካ የነበራቸውን አመለካከት በመለወጥ ብዙ ውጤቶችን አስከትሏል፡፡

በዋነኛነት ኢትዮጵያ በዘመኑ የአውሮፓን ቅኝ ገዢ ሀገር በጦርነት ድል ያደረገች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር አድርጓታል።

አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ የነበራቸው አመለካከትም ተቀይሯል፡፡

አውሮፓውያን አፍሪካውያንን በቁም ነገር መመልከት የጀመሩት ከዓድዋ ድል በኋላ ነበር ሲሉ ነው ዕውቁ የታሪክ ምሁር ሬይመንድ ጆናስ የጻፉት፡፡

ሬይሞንድ እንደጻፈው ምንም እንኳን የዘረኝነት አመለካከቶች ባይወገዱም ድሉ የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ሥርዓት ፈታኝነትን በመቀነስ ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ሕዝቦችን አስከብሯል።

በፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሀሳብ ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ የአፍሪካውያንን የነጻነት እንቅስቃሴዎች አነሳስቷል።

የታሪክ ምሁሩ ሬይሞንድ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በኅብረት መዝመታቸው እና የባለቤታቸውን የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጠንካራ ድጋፍ መጠቀማቸው ሀገራቸው ለድል እንድትበቃ አድርጓቸዋል ሲል መስክሯል፡፡

የዓድዋ ድል ውጤቶች:-

ለዘመኑ የጣሊያን መሪዎች ሽንፈትን አስከትሎ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አጽንቷል፡፡ ከአድማስ ተሻግሮም በዓለም ዙሪያ ጉልህ ተጽዕኖ አስከትሏል።

በጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ እንዲነሳ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ጥቁሮች ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መነቃቃትንና ተስፋን ፈጥሮ ነበር፡፡

በአጠቃላይ የተገኙ ውጤቶችን ስናይ፡-
• የዓድዋ ጦርነት ምክንያት የነበረው የውጫሌ ስምምነት ውድቅ ሆነ፤
• ጣሊያን የኢትዮጵያን ነጻ ሀገርነት ተቀብላ የአዲስ አበባውን ስምምነትን ፈረመች ፤
• አውሮፓውያንን የሚገዳደር ኃይል ሊፈጠር እንደሚችል አሳየ፤
• ኢትዮጵያ ለነጻነት ትግል ቀንዲል ሆና እንድትታይ አደረገ፤
• አፍሪካን በተቀራመቱ ቅኝ ገዢዎች ላይ ስጋትን ፈጥሯል፤
• ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የኃያልነት ትርክት ቀየረ፤
• የጣሊያኑ የፍራንሲስኮ ክርስፒ አስተዳደር እንዲወድቅ ምክንያት ሆነ፤
• ጦርነቱን ለመራው ጀነራል ባራቲየሪ ውድቀት ሆነ፤ ለሽንፈቱም ክስ ተመስርቶበት ነበር፤

Exit mobile version