Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዓድዋ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ተጋድሎ ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ሊረዳው ይገባል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓድዋ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመጠበቅ ያደረጉትን ተጋድሎ ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ሊረዳው ይገባል አሉ ምሁራን፡፡

በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ጸጋዬ ሞረዳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የአሁኑ ትውልድ እንደቀደሙት ኢትዮጵያውያን ሀገርን በማስቀደም ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ የሚተርፍ መልካም ስራ መስራት አለበት፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሩን ለመጠበቅ በዓድዋ ጦርነት ላይ በመሳተፍ አኩሪ ገድል መፈጸሙን አስታውሰው፥ በዚህ ዘመን ያሉ ኢትዮጰያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጀምሮ በመጨረስ ዳግማዊ ዓድዋን በሌላ ዘርፍ መድገም ችለዋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተሰማራበት መስክ ለሀገር የሚጠቅምና ለቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገር ታሪክ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ታሪክን ለትውልድ ከማስተማርና ከማስተላለፍ አንጻር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፥ ዓድዋ ጥቁር ሕዝብ በአጠቃላይ የሚኮራበት ድል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዘርፉ የተማረ በርካታ ወጣት ኃይል እንዳላት ጠቁመው፥ የዚህ ዘመን ትውልድ በተለያዩ ዘርፎች ጠንክሮ በመስራት እንደቀደሙት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የራሱን ታሪክ መጻፍ አለበት ነው ያሉት፡፡

ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት የማያግባቡ ጉዳዮችንና ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፥ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የወጣቱ ትውልድ አንድነትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዓድዋ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ መስዋትዕነት ከፍለዋል ያሉት ደግሞ በመከላከያ ጦር ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር አየለ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ትወልዱ በተሰማራባት መስክ ስራውን በአግባቡ በመስራት ለሀገሩ ዕድገት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ገልጸው፥ ትውልዱ ስለ ድሉ ግንዛቤ እንዲኖረው በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት ትውልድን በማነጽ ለአዲስ ታሪክ አንዲዘጋጅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ምሁራን አመልክተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version