1. የጠቅላላ ምርጫ ምዝገባ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቦርዱ በሚወስናቸው ቀናት የሚጀመርና የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
2. ቦርዱ የሚመለከታቸውን ክልሎች ሕገ መንግስት ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች መነሻ በማድረግ የአካባቢ ምርጫዎችን የምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ ያወጣል፡፡
3. ቦርዱ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) እና (2) መሠረት የምዝገባ ቀናቱን ከመወሰኑ በፊት በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንደ አስፈላጊነቱም ከሲቪል ማህበራት፤ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይመካከራል፡፡
4. ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምርበትን ዕለት በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው በማካተት ምዝገባው ከመጀመሩ 15 ቀን በፊት ጀምሮ ባሉት ቀናት በተከታታይ በመገናኛ ብዙሃንና በሌሎች የማስታወቂያ መንገዶች አማካኝነት የምዝገባውን ሰሌዳ ለህዝቡ ይገልፃል፡፡
5. የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በፌደራል መንግስት ህጎች የተደነገጉ የሕዝብ በዓላትን ሳይጨምር በመደበኛ የመንግሥት የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት መሰረት ይከናወናል፡፡
6. የምርጫ አስፈጻሚዎቹ የየክልሉን መደበኛ የሥራ ሰዓት በመከተል ለአንድ ሰዓት ብቻ ለምሳ ይወጣሉ፡፡
7. ቦርዱ በአንዳንድ ክልሎች ያለውን የመንግሥት የስራ ሰአት አፈፃፀም ህጎች ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ ሆኖ ሲያገኘው የተለየ የስራ ሰዓት ሊወስን ይችላል።

