አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥቅም በመመሳጠር መንግሥትን ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ያሳጡ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሾች በጉምሩክ ኮሚሽን የደወሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሠራተኛ የሆኑት 1ኛ አማኖ መገርሳ ገልገሎ፣ 2ኛ አብነት ደምስ አየነው እና በግል ሥራ የሚተዳደረው 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ግርማ ደስታ ናቸው።
1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በደወሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ እና የስካኒንግ ማሽን ምስል ትንተና ባለሙያ ሆነው ተመድበው ይሰሩ ነበር፡፡
በዚህ ወቅትም ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ታሕሳስ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በ3ኛ ተከሳሽ አስመጪነት 595 የልብስ ማጠቢያ በሚል ሰነድ ከጂቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ 2 ሺህ 229 ቴሌቪዥኖች በስካኒንግ ማሽን ዕቃዎቹ ዝርዝር ፍተሻ ሳይደረግ በስካኒንግ ማሽን ተፈትሿል በሚል የማረጋገጫ ማሕተም በመምታት ጭምር በልብስ ማጠቢያ ማሽን ስም ቴሌቪዥኖቹ እንዲያልፉ ማድረጋቸው ተጠቅሶ በየተሳትፎ ደረጃቸው መከሰሳቸው ተመላክቷል፡፡
በ3ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበው 2ኛ ክስ ደግሞ በሕጋዊ ሽፋን ምንም አይነት ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸውን ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በማሰብ በዲክላራሲዮን የተመዘገበው የልብስ ማጣቢያ ማሽን ነው በሚል 2 ሺህ 229 ቴሌቪዥኖች አስገብቶ ተገኝቷል የሚል ነው፡፡
በዚህም ለመንግሥት መክፈል የነበረበትን ከ125 ሚሊየን ብር በላይ ታክስ እና ቀረጥ በማሳጣት በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ የጉሙሩክ ማጭበርበር ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ተከሳሾቹ ተዘጋጅተው በክሱ ላይ ለመቅረብ በጠየቁት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት በይደር ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ

