አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሳምንት ከሚያዚያ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
መርሐ ግብሩ “ኢትዮጵያ ትገነባለች! ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት ለመሠረተ ልማት እምርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ነው የሚከናወነው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በሰጡት መግለጫ÷ ሳምንቱ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ የተገኙ ተሞክሮዎችን ለመተንተንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ያለመ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪውን የሀገር ውስጥ ምርት አቅም ለማሳደግ፣ የተቋማትን ቅንጅታዊ አሠራር ለማሳለጥና አዳዲስ የግንባታ ዘዴዎችን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ በዘርፉ ላይ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና አስፈጻሚ ተቋማት ዕውቅና የሚያገኙ ሲሆን÷ መድረኩ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በማነቃቃት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ወደ 40 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ አዳዲስ መንገዶችን በመገንባት የመንገድ ርዝመትን ከ44 ሺህ ወደ 182 ሺህ ኪሎ ሜትር ማሳደግ መቻሉ ተመላክቷል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ

