አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)::
ሚኒስትሯ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ”የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓሉ ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚዳስስ መልኩ እንደሚከበር ተናግረዋል።
አከባበሩ የሴቶችን መብቶች ወደ ተጨባጭ የኑሮ ለውጥ በመቀየር የሴቶችን የሐብት ክፍፍል፣ የማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሴቶች ተሰርተው የመጡ ድሎችን ማስቀጠልና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያን ሴቶች ብልጽግና ማረጋገጥ ላይ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ባለፉት 50 ዓመታት ሴቶች እንዴት ተጠቃሚ ሆኑ፣ የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችስ ምንድናቸው የሚለውንና ሌሎች ሥራዎችን የሚዳስስ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ለአብነትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት መቻሉን አንስተዋል።
እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የካቢኔ አባላት ሆነው ቁልፍ ሴክተሮችን እንዲመሩ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን ላይ ሴቶች 41 በመቶ የሚሆነውን መቀመጫ አግኝተው የወከላቸውን ማሕበረሰብ እያገለገሉ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በማሕበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በአካባበሩ 30 ሚሊየን ሴቶች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲወስዱ እንዲሁም የጡትና የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

