Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርም ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኅብረተሰቡ መረጃ የሚቀበልበትና ሌሎችም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርም ይፋ አድርጓል።

አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ከመደበኛው ድረ-ገጽ በብዙ ገፅታዎቹ የሚለይ የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርም በውስጥ አቅም አበልጽጓል።

ፕላትፎርሙ ዜጎች በፀጥታ፣ በደኅንነትና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ከየትኛውም ስፍራ ሆነው መረጃ የሚሰጡበት የሪፖርት ማድረጊያ ክፍል እንዳለው ገልጿል።

ሀገራዊ የደኅንነት፣ የመረጃና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተም ወቅታዊ መረጃዎችን ያጋራል ብሏል።

የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የስጋት ተጋላጭነትን የተመለከቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ኅብረተሰቡም ሆነ የውጭ ዜጎች መረጃውን በመጠቀም በየትኛውም ስፍራ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማገዝ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል፡፡

የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ ለወደፊቱ የተቋሙን መስፈርት የሚያሟሉና ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ዜጎች አገልግሎቱን በመቀላቀል ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችል የማመልከቻ ገጽ የተካተተበት ነው።

የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ አገልግሎቱ እያከናወነ በሚገኘው ሪፎርም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ በማበልፀግ የላቀ የመፈፀም አቅም ያለው ተቋም ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል፡፡

ዜጎችም ተዓማኒነት ያላቸውና ተጨባጭ መረጃዎችን በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ለማሳካት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የደኅንነት ተጋላጭነት ፍተሻ ተደርጎለት የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው የአገልግሎቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

Exit mobile version