Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህፃን ብሌን አስፈላጊውን ህክምና እንድታገኝ የ4 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት 10 ዓመታት በከፍተኛ የአንጎል ውስጥ ውሃ እና የአንጎል ግፊት መጨመር (ሀይድሮሴፋለስ) ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ለሆነችው ህፃን ብሌን አሸናፊ ህክምና እንድታገኝ የ4 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደርገናል አሉ፡፡

የገንዘብ ድጋፉ ህፃን ብሌን ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ አስፈላጊውን ህክምና እንድታገኝ የሚያስችል ነው።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ፤ በህፃን ብሌን መኖሪያ ቤት ተገኝተው እንደጎበኟት ገልጸዋል።

ህጻን ብሌን ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ አስፈላጊውን ህክምና እንድታገኝ በሀኪሞች ቢታዘዝላትም በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እስካሁን ህክምና ሳታገኝ መቆየቷን አስታውሰው፤ ለህክምናዋ የሚያስፈልገውን 4 ሚሊየን ብር ለወላጅ አባቷ አስረክበናል ነው ያሉት።

ድጋፉ ለከተማችን ነዋሪዎች ችግር መቃለል ሁሌም እንደምናደርገው ድጋፍ አካል ነው ብለዋል።

የብሌን አባት ወጣት አሸናፊ በከተማዋ በጽዳት ሰራተኝነት ተቀጥሮ እየሰራ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወጣቱ ያለ እናት እርዳታ ብሌንን፣ ታናሽ እህቷን፣ ሌላኛዋን አካል ጉዳተኛ እህቱን እና በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ አገልግለው ጡረታ የወጡ አቅመ ደካማ እናቱን የሚንከባከብ፣ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ጠንካራ ሰው መሆኑን ገልጸዋል።

ህፃን ብሌን የታዘዘላትን የፊዚዮቴራፒ ህክምና እንድትከታተል በአሁኑ ወቅት የሚኖሩበት ቤት የማይመችና ከህመሟ ባህሪ አንጻር እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ቤተሰቡ የተሻለ መኖሪያ ቤት እንዲያገኝ ወስነናል ብለዋል።

የብሌንን አጠቃላይ የህክምና ወጪ ለሸፈኑት ለሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች፤ የህፃን ብሌን ፈገግታዋ ተመልሶ፣ እንደ እኩዮቿ የምትቦርቅበት እና ትምህርት ቤት የምትሄድበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን ተመኝተዋል።

Exit mobile version