አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያቀረበው “ምርጫችን ነው – ሀገር ያለ እኛ” የተሰኘ ህብረ ዜማ ተመርቋል።
ህብረ ዜማው ምርጫ ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና፣ የአንድ ድምፅን ኃይልና ዜጎች በመብታቸው በመጠቀም ለሀገራቸው ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ የሚገልጽ ኪነ ጥበባዊ ሥራ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀው ህብረ ዜማ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ለህዝብ ተደራሽ ይሆናል።
ህብረ ዜማው የመራጮችን ተሳትፎ ለማነቃቃት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ቦርዱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ቁሳቁስ ስርጭትና የአስፈጻሚዎች ስልጠና እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ እንደሚጀመር ጠቅሰው፤ ዜጎች በቦርዱ መተግበሪያ አልያም በአካል በሚደረጉ የቴክኖሎጂ ምዝገባዎች ተጠቅመው እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በአንዱአለም ተስፋዬ

