አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሞጆ ሐዋሳ ፕሮጀክት አካል የሆነውና ምዕራፍ 3 የባቱ – ነጌሌ አርሲ ፈጣን መንገድ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው አለ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፡፡
በአስተዳደሩ የሞጆ ሐዋሳ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት ቡድን መሪ ደፋሩ ደረሰ (ኢ/ር) እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ በ5 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ሲሆን የስራ ሂደቱ 99 በመቶ ተጠናቅቋል።
ፕሮጀክቱ 57 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለውና የጎን ስፋቱም 31 ነጥብ 6 ሜትር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያነት የሚውለው ወጪ በዓለም ባንክ የተሸፈነ ሲሆን÷ ግንባታው በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ተቋራጭ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
የሞጆ ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ፕሮጀክት የጉዞ ሰዓትን በግማሽ የሚቀንስና የአዲስ አበባ – ሞጆ – ሞያሌ – ላሙ – ሞምባሳ ትራንስ ኢንተርናሽናል ሐይዌይ አካል መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
10 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ኮሪደር (ኬፕታውን ትራንስ አፍሪካን ሐይዌይ) አካል ስለመሆኑም ተጠቁሟል።
በዚህም የአሕጉሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ትስስር ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ከመሆን ባሻገር የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ምቹ በማድረግ ለቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በታምራት ደለሊ

