Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ሕዝብ ለሕወሓት ባለመገዛት ክልሉን ከገባበት ውስብስብ ችግር መታደግ አለበት – የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ሕዝብ ለሕገ ወጡ ቡድን ሕወሓት አልገዛም በማለት ክልሉን ከገባበት ውስብስብ ችግር መታደግ አለበት አሉ የትግራይ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ትዴፓ) ዋና ፀሐፊ ሙሉብረሃን ኃይሌ እንዳሉት÷በክልሉ የሚገኘው ሕገ ወጥ ቡድን ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆንና ጠቅላላ ምርጫው በክልሉ እንዳይካሄድ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

የሀገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማያከብር ቡድን ይህን ያህል ዕድል መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው ÷ ቡድኑ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሉዓላዊት አደጋ እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

የስምረት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃለፎም ነርዐ በበኩላቸው ÷ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብና ክልሉ የልማት ተቋዳሽ እንዳይሆን ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ሕግ እንዲከበርና በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች ተወካዮቻቸውን መምረጥ እንዲችሉም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር መቆም እንዳለበት ግንዛቤ እየፈጠርን ነው ያሉት ደግሞ የሰባ እንደርታ ፓርቲ ሊቀመንበር ከበደ አሰፋ ናቸው።

የትግራይ ሕዝብ ለሕገ ወጡ ቡድን አልገዛም በማለት ክልሉን ከገባበት ውስብስብ ችግር መታደግና እንደ ሁልጊዜው የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር የድርሻውን እንዲወጣ የፓርቲ አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተካልኝ ሃይሉ

Exit mobile version