Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

6ኛው ሀገራዊ የጎዳና ላይ ኢፍጣር የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው ሀገራዊ የጎዳና ላይ ኢፍጣር የፊታችን ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል አለ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፡፡

ሀገራዊ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብሩ “ነጃሺ ለሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው፡፡

የጠቅላይ ም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር እንዳሉት÷ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ሥነ ሥርዓቱ ኢስላማዊ እሴቶች የሚጎለብቱበትና አብሮነታችንን የምናሳይበት ነው።

በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ቀን የሚከናወነው መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ለእስልምና ያላትን ውለታ በሚያንጸባርቅና በሚመጥን መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመው÷ ተሳታፊዎች የእስልምና ሥነ ምግባርን እና የረመዳን ጾምን ታላቅነት በጠበቀ መልኩ መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኡስታዝ አቡበከር ሕዝበ ሙስሊሙ በስፍራው በመገኘት መርሐ ግብሩን እንዲካፈል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት እና በኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ትብብር ነው የሚዘጋጀው፡፡

በመራኦል ከድር

Exit mobile version