አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ኩራትና ገጽታ ቀይሯል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ ከኡራኤል – ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል የሚያገናኘው የኮሪደር ልማት ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት የሚያጎናፅፉና ለሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተካትተውበት ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡
መስመሩ ከዚህ በፊት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የአስፋልት መንገዶች የነበሩበት፣ የእግረኛ መንገድ እጥረት የሚስተዋልበት፣ የሳይክል መንገድ የሌለው፣ ከፍተኛ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር የነበረበትና ደረጃውን የጠበቀ የስዌሬጅና የድሬኔጅ መስመር ያልነበረው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
እንዲሁም እንደ ሸረሪት ድር የተወሳሰቡ የኤሌትሪክና የቴሌኮም ገመዶች የሚታዩበት፣ የደህንነት ካሜራዎች፣ የስፖርት ሜዳዎችም ሆኑ የሕፃናት መጫወቻዎች ያልነበሩበት እና የሕንፃዎች ውበት በቆሻሻና ዕድሳት በማጣት እንዲሁም አላስፈላጊ በሆኑ ተለጣፊ ግንባታዎች ተሸፍኖ የቆየ ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ ግን በመዲናዋ በተከናወነ የኮሪደሪ ልማት ሥራ አካባቢው ለአይን ማራኪ እና ዘመናዊ መልክ ይዟል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ 5 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ የትራንስፖርት ተርሚናል፣ የእግረኛና የሳይክል መንገድ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ጣቢያ፣ የንግድና መዝናኛ ስፍራዎች፣ አረንጓዴ ልማትና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራን አካትቷል፡፡
በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም ዘመናዊ መብራት እና የደህንነት ካሜራዎች እንዳሉት አስገንዝበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት መደረጉን ነው ከንቲባዋ ያስረዱት፡፡
ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የንግድ እንቅስቃሴውን በእጅጉ ማነቃቃቱን ጠቁመው÷ ወደፊት የተሻለ ውጤት እንደሚገኝበት አመልክተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

