አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ 5ኛ ዙር የኤፍ ኤ ዋንጫ ዛሬ ኒውካስል ዩናይትድ ከማንቼስተር ሲቲ፣ አርሰናል ከማንስፊልድ ታውን እንዲሁም ቼልሲ ከሬክሳም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም በማቅናት ምሽት 5 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ዓመት ብቻ ለ5ኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን÷ በቅርቡ በተገናኙበት የካራባኦ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ማንቼስተር ሲቲ በደርሶ መልስ አሸንፎ ለፍጻሜ መድረሱ ይታወሳል፡፡
ለአራቱም ዋንጫዎች እየተፎካካረ የሚገኘው ሲቲ ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል በሚያደርገው ጉዞ ከኒውካስል ጠንካራ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡
ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ለአራቱም ዋንጫዎች እየተፋለሙ የሚገኙት መድፈኞቹ በዋን ኮል ስታዲየም ቀን 9 ሰዓት ከ15 ላይ ከማንስፊልድ ታውን ይጫወታሉ፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በኤፍ ኤ ዋንጫ ሲገናኙ የዛሬው ከ95 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን÷ አርሰናል በመድረኩ በእንግሊዝ 3ኛው የሊግ እርከን ከሚገኙ ቡድኖች ያደረጋቸውን ያለፉት 15 ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል፡፡
ቼልሲ በበኩሉ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ወደ ሩብ ፍጻሜው ለመቀላቀል ከሬክሳም ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
በአቤል ነዋይ

