አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የረመዳን ወርን ከድሆች፣ ችግረኞች እና ስደተኞች ጋር በጋራ በመብላት፣ በመጠጣትና በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል አሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ።
6ኛው ሀገራዊ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ሼኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አንድነትን በተግባር የሚያሳየው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር አስደሳች መሆኑን ገልጸው÷ የረመዳን ወር የቸርነት ወር በመሆኑ ከድሆች፣ ችግረኞችና ስደተኞች ጋር በጋራ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮች ለሀገራችን፣ ለወገናችን፣ ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም ዱዓ ማድረግ ይገባል ያሉት ሼኽ ሐጅ ኢብራሂም÷ ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ ሀገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት በመሆኑ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን መሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር በበኩላቸው÷ ይህች ሀገር ሁላችንም ስንሳተፍበት ነው ልታድግ የምትችለው፤ ልማቱ፣ እድገቷ፣ ብልጽግናዋ የእኛው ስለሆነ የሁላችንንም ተሳትፎ ይሻል ብለዋል።
ነገን የተሻለ ለማድረግ ለሚሰሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሙስሊሙ ማሕበረሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከተማ መስተዳደሩን የየጸጥታ አካላትን እና ለኢፍጣር መርሐ ግብሩ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሐይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በዮናስ ጌትነት

