አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ641 ሺህ በላይ ወጣቶች እየተሳተፈ ነው አለ የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ማርቆስ ማቲዮስ በክልሉ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 የተለያዩ ዘርፎች አየተካሄደ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም በአካባቢ ጥበቃ ስራና በክረምት ወራት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸርን የሚቀንሱ እና የተፋሰስ ልማትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት የማደስና እንደ አዲስ የመገንባት፣ የወጣት ስብዕና ማዕከላትን የማጠናከርና በቁሳቁስ የማደራጀት፣ የከተማ ጽዳትና ውበት ስራዎች ላይም በመሳተፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።
በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የማሕበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ አሁን ላይ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በዚህም ስራ እስካሁን ከመንግሥት እና ከማሕበረሰቡ ሊወጣ የነበረውን ከ610 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏልም ነው ያሉት።
ወጣቶቹ ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የተለያዩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዮናስ ጌትነት

