አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ‘የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው በዓሉ ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚዳስስ መልኩ እንደሆነ ተገልጿል።
አከባበሩ የሴቶችን መብቶች ወደ ተጨባጭ የኑሮ ለውጥ በመቀየር የሴቶችን የሀብት ክፍፍል፣ የማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ አተኩሯል።
በተጨማሪም በሴቶች ተሰርተው የመጡ ድሎችን ማስቀጠልና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ሴቶችን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቃል የሚገባበት እንደሆነም ተመላክቷል።
ባለፉት 50 ዓመታት ሴቶች እንዴት ተጠቃሚ ሆኑ፣ የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችስ ምንድናቸው የሚለውንና ሌሎች ሥራዎችን የሚዳሰሱበት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የተቻለ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ተችሏል።
እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የካቢኔ አባላት ሆነው ቁልፍ ሴክተሮችን እንዲመሩ ተደርጓል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን ላይ ሴቶች 41 በመቶ የሚሆነውን መቀመጫ አግኝተው የወከላቸውን ማሕበረሰብ እያገለገሉ ነው።
በማሕበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

