አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ( ማርች 8 ) ሲከበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ በማድረግ ቀኑን ያከብራል።
ይሄ የአየር መንገዱ ተግባር በእንቅስቃሴው ሁሉ ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ እንዳላቸው ያሳያል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ( ማርች 8 ) ‘የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው በዓሉ ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚዳስስ መልኩ ነው።
አየር መንገዱም ይህንን መሪ ቃል በሚገልጽ መልኩ ቀኑን እያከበረ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት በሴት ካፒቴኖች የሚመሩ ስምንት በረራዎችን ያደርጋል።
በዚህም ወደ ፍራንክፈርት፣ አክራ፣ ሙምባይ፣ ካይሮ፣ ጂቡቲ፣ ናይሮቢ፣ ዊንድሆክ እና ድሬዳዋ ከተሞች በሴት ካፒቴኖች የሚመሩ ይደረጋሉ፡፡
በአቪዬሽን ዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ለማላቅ እየሰራ እንደሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ÷ ከጠቅላላ ሰራተኞቹ ውስጥ የሴቶች ድርሻ 40 በመቶ እንዲሁም በአመራር ቦታዎች ደግሞ 35 በመቶ ነው።
በተጨማሪም ለሴቶች ዝግ ሆኖ የቆየው የአብራሪነት ሙያን በር በመክፈት አየር መንገዱ 95 ሴት አብራሪዎችን አፍርቷል።

