አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷አሁን ላይ በክልሉ 12 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከመማሪያ መጽሐፍ አቅርቦት ጋር በተያይዘ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ አንደኛ ደረጃ ላይ ግን እጥረት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 5 ነጥብ 4 ሚሊየን የአንደኛ ደረጃ መማሪያ መጽሐፍት ታትሞ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የሚሰጠው የት/ቤት ምገባ አገልግሎት የተማሪዎችን የመቅረት ምጣኔ ከመቀነስ ባለፈ ለአዕምሯዊና አካላዊ እድገታቸው አዎንታዊ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ 6 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የምገባ አገልግሎቱ በሁሉም አካባቢዎች ወጥነት እንዲኖረው ለማስቻል በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማሳደግም የመምህራንን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
የመምህራንን ጥቅም ከማስከበር አንጻር የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተከናወነው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
በሕብረተሰብ ተሳትፎ አዳዲስ ት/ቤቶችን መገንባት እና የነባሮችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ከተማሪዎች እና መምህራን ሥራ በተጨማሪ ወላጆች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

