Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዜጎች በአንጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት የመሳተፋቸው አስፈላጊነት

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በእስካሁኑ ጉዞው ከትግራይ ክልል በስተቀር በ11 ክልሎች፣ በ2 የከተማ አስተዳደሮች፣ ከፌዴራል ተቋሟት እንዲሁም በዲያስፖራው ማሕበረሰብ ዘንድ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳ ማሰባሰብ ችሏል፡፡

መደበኛ ባልሆነ መልኩ ደግሞ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን በአካል በመቅረብ ወይም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ለኮሚሽኑ እያስገቡ ይገኛሉ፡፡

በዚህ መነሻነት በሀገራዊ ምከክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋችው ለምን አስፈለገ? የትኞቹን ውጤቶች እንዲያመጣስ ይጠበቃል?

👍አካታች የሆነ ውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ
በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ ከዜጎች የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ በሂደቱ ሁላችንም ሃሳባችንን ለማቅረብ በንቃት መሳተፋችን ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ በሀገራችን ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለመጫወት በር ይከፍትልናል፡፡

👍የዜጎችን ጥያቄዎች ለመረዳት
በሀገራዊ ምክከር ሂደት ውስጥ በዜጎች እና ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ የአጀንዳ ሃሳቦች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ስሜት እና ፍላጎት እንዲያንፀባርቁ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ መንገድ ከፋች ነው፡፡

👍ድምፃቸው ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማስተናገድ
የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሃሳቦችን ለማስተጋባት መደላድል ይፈጥራል፡፡ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለተካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው ሀሳባቸውን ማቅረባቸው በሀገራችን የዲሞክራሲ ልምምድ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

👍ዜጋ-ተኮር መፍትሔዎችን ለማመንጨት
የሀገራዊ ምክክር ሂደት ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ዜጎች ሃሳቦቻቸውን በቀጥታም ይሁን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሲያቀርቡ በሂደቱ ሊኖራቸው የሚገባው የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ መንገዱን ይጠርግላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ዜጎች የጉዳዩ ማዕከል ሆነው በሀገራዊ ምክክሩ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሃሳቦችን በጋራ ማመንጨት ይችላሉ፡፡

👍 መተማመንን እና ማህበራዊ ትስስርን ለመገንባት እና ለማደስ
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በእውነት እና በግልፅ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ማቅረባቸው የጋራ መተማመንን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በሂደቱም ሀሉም አካላት ካለፈው ተምረው ስለ ነገዋ የጋራ ሀገራቸው መክረው የማህበራዊ ውሎቻቸውን ያድሳሉ፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ በመደበኛ መልክ አጀንዳዎችን የሚሰበስብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ቢነሳልኝ የሚሉትን አጀንዳ/ዎች በቡድን ወይም በግል ከታች በተቀመጡት አድራሻዎች ማቅረብ ይችላሉ፡፡

👍የአጀንዳ ሀሳብዎትን ለመስጠት
ከአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ በሚገኘው የኮሚሽኑ ፅ/ቤት በፅሁፍ ማስገባት ይችላሉ፡፡
በፖስታ ሳጥን ቁጥር፡ 32623 አዲስ አበባ
በኢሜል፡ ethiopianndc@gmail.com
በኮሚሽኑ ድረ-ገፅ፡ https://ethiondc.org.et መጠቀም ይችላሉ፡፡

Exit mobile version