አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ግዙፍ የኔትወርክ ማስፋፊያዎችን ለማከናወንና ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ከዜድ ቲ ኢ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምመነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከዜድ ቲ ኢ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ኢኒሸቲቩ 647 የኔትወርክ ጣቢያዎችን የሚያካትት ሲሆን÷ የኔትወርክ ተደራሽነት ለማሳደግና የኢትጵያን የዲጂታል አካታችነት ይበልጥ ለማስፋፋት የላቀ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የ4ጂ የሕዝብ ሽፋንን ወደ 95 ነጥብ 5 በመቶ በማሳደግ የኔትወርክ አቅምን ተደራሽነትና የአገልግሎት ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ያስችላል፡፡
በተለይም ዘመናዊ የሞባይል ብሮድባንድ ኢንተርኔትን ወደ ገጠርና አገልግሎቱ ወዳልተዳረሰባቸው አካባቢዎች በማዳረስ የኢትዮጵያን የዲጂታል አካታችነት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ስምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ሰፊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ለመደገፍና የዲጂታል ሥነ ምህዳሩን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መጠቀሱን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡
ግዙፍ የኔትወርክ ማስፋፊያ ስምምነቱ በባርሴሎና በተካሄደው የ2026 የሞባይል ዓለም አቀፍ ኮንግረስ ጎን ለጎን መፈረሙ ተገልጿል፡፡

