አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት መደረግ ይጀምራሉ፡፡
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከጋላታሰራይ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፤ ጋላታሰራይ ሦስቱን ሲያሸንፍ ሊቨርፑል በአንዱ ድል አድርጎ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት በመድረኩ ተገናኝተው ጋላታሰራይ በቪክቶር ኦሲሜን ብቸኛ (የፍጹም ቅጣት ምት) ግብ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ምሽት 5 ሰዓት ላይ ኒውካስል ዩናይትድ በሜዳው ሴንትጀምስ ፓርክ ባርሴሎናን ያስተናግዳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በመድረኩ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና አራቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኒውካስል ዩናይትድ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ሌላኛው የእንግሊዝ ተወካይ ቶተንሃም ሆትስፐር ወደ ስፔን አቅንቶ አትሌቲኮ ማድሪድን ይገጥማል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐር በሻምፒየንስ ሊጉ የተሻለ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
የ16ቱ ጥሎ ማለፍን የተቀላቀለ ብቸኛው የጣሊያን ክለብ የሆነው አታላንታ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሜዳው ባየርን ሙኒክን ያስተናግዳል፡፡

