Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ፕሬዚዳንት ፑቲን በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።

የክሬምሊን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ እንዳሉት፤ መሪዎቹ በኢራን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን ሁኔታ በድርድር ለመፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት ውጤታማ እንደነበር የክሬምሊን መረጃ ጠቁሟል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን ከኢራን ጋር የተፈጠረውን ግጭት ማስቆም የሚቻልበት የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረባቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን እያካሄዱ ስላለው ዘመቻ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን ግጭት አስመልክቶ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፍላጎት እንዳላቸውም በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።

ሁለቱ መሪዎች ስለ ነዳጅ ዋጋ እና ቬንዙዌላ አጠቃላይ ሁኔታ መምከራቸውን የክሬምሊን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭን ዋቢ አድርጎ አናዶሉ ዘግቧል።

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version