አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱ የንግድ እንቅስቃሴን ያዳከመ ሳይሆን ከተማዋን ለንግድ ስራ ቀላል፣ ሳቢና ምቹ ያደረገ ነው አሉ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት፥ በኮሪደር ልማት ስራው ከተገነቡ አዳዲስ ሱቆች በተጨማሪ ነባሮቹን ከመንገድ ወደ ኋላ በመሳብ መልሶ የመገንባት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የኮሪደር ልማትና የመልሶ ማልማት ስራው አነስተኛ ቢዝነሶችን የሚያዳክም አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፥ የንግድ ተቋማት ይበልጥ ዘመናዊ፣ ለስራና ለሸማቹ ሳቢ በሆነ መንገድ እንዲገነቡ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም 2 ሺህ 800 የንግድ ሱቆች እንደ አዲስ የተገነቡ ሲሆን፥ 2 ሺህ 690 ያህል ሱቆች ከመንገድ ወደ ኋላ በመሳብ በነበሩበት አካባቢ በአዲስ መልክ ደረጃቸውን በማሻሻል ተገንብተዋል ነው ያሉት፡፡
55 በመቶ የሚሆነው ግንባታ በንግድ ተቋማቱ ባለቤቶች የተከናወነ ሲሆን፥ ቀሪውን መንግስት ገንብቶ ለልማት ተነሺዎች ያስረከባቸው መሆናቸውንም ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡
መሬት ለመውሰድ ፍቃደኛ የሆኑትን በአክሲዮን ማህበር ተደራጅተው እንዲገነቡ እያደረግን ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ የኮሪደር ልማት ስራው የቢዝነስ እንቅስቃሴውን ያዳከመ ሳይሆን ከተማዋን ለንግድ ስራ ቀላል፣ ይበልጥ ሳቢና ምቹ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ለአብነትም ቀደም ሲል ከቦሌ አትላስ እስከ ብራስ ባለው መንገድ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ተነስተው የነበሩ የንግድ ተቋማት በትናንትናው ዕለት በይፋ ክፍት በተደረገው የድል ፕላዛ ውስጥ ስራቸውን በስኬት ጀምረዋል ነው ያሉት።

