አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቻይናን የዶክመንተሪና የካርቶን ፊልሞች እንዲሁም ድራማዎችን ለማስተላለፍ ከቻይና ሚዲያ ግሩፕ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ልዩ መልክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ቼን ሃይ ፊልሞቹን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስረክበዋል።
አምባሳደር ቼን ሃይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ድራማዎቹ የኢትዮጵያ እና ቻይን የህዝብ ለህዝብ ትብብር ለማጠናከርና የባህል ልውውጥ ለማድረግ ያግዛል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የፈጠረው ጠንካራ የሚዲያ አቅምና ከቻይና የሚዲያ ተቋማት ጋር የደረሰበት የግንኙነት ደረጃ ዶክመንትሪዎችና ድራማዎቹን ለማስተላለፍ ተመራጭ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ሚዲያዎች የሀገራትን ባህል፣ ስልጣኔ፣ ልማትና የስራ ልምድ በሀገራት መካከል ለመጋራት ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው፥ ፋና የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ ፋና ባሉት የሚዲያ አውታሮች ኢትዮጵያን ለማብሰር ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የቻይናን ፊልሞች ማስተላለፉ የኢትዮጵያ እና ቻይናን ግንኙነት ከማሳደግ በተጨማሪ ለተቋሙ የቴክኒክ፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍና የእውቀት ሽግግር እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብሪክስ ፕላስን ጨምሮ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል
በዓለምሰገድ አሳዬ

