አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ምርትን አላግባብ በሚያከማቹና በሚደብቁ አካላት ላይ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰዳል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ይመር ዳውድ የቡና ምርትና ዓለም አቀፍ የገበያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ይመር በመግለጫቸው ቡና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም የወጪ ንግድ ዕቅድ የተያዘለትን ግብ በኤክስፖርት መጠን ለማሳካት ተግዳሮቶች እንደገጠሙት አንስተዋል።
በግማሽ ዓመቱ 200 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 35 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን÷ ይህም በገቢ ረገድ ከዕቅዱ በላይ አፈጻጸም የታየበት ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአፈጻጸም ሲታይ በመጠን 74 በመቶ ብቻ ማሳካት እንደተቻለ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
ለዚህ ከዕቅድ በታች አፈጻጸም ዋነኛው ምክንያት የምርት ክምችት እንዲሁም የዶላር ምንዛሪ ይጨምራል የሚል የተሳሳተ ግምት ተጠቃሽ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ወቅታዊ የቡና አቅርቦትን ለዓለም ገበያ ማረጋገጥ፣ ምርት እንዳይሸሸግ ግንዛቤ መፍጠር እና ምርት በሚሸሽጉ አካላት ላይ ጥብቅ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ መናገራቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

