Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ውስጥ የማይፈታ ጥያቄና ችግር የለም – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በንግግር እና በምክክር የማይፈታ ጥያቄም ሆነ ችግር የለም አሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፡፡

ኮሚሽነሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኮሚሽኑ እስካሁን ባካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብና መቅረጽ ሒደት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈቱ የማይችሉ ጥያቄዎችም ሆነ ችግሮች እንደሌሉ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሚነሱ ችግሮች በኢትዮጵያ ጥላ ስር ያሉ በመሆናቸው በዜጎች ምክክርና ንግግር መፈታት የሚችሉ ናቸው በማለት ገልጸው÷ አሁን መመለስ የማይችሉ ጥያቄዎች ቢኖሩ እንኳን በጊዜ ሒደት መፈታት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሌሎች ሀገራት ልምድ መቅሰሙን አንስተው÷ ያልተሳኩ ምክክሮች በውስጥና በውጭ ጣልቃ ገብነት መሆኑን መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ኮሚሽኑ ከሀገር ውስጥ፣ ከመንግሥት እንዲሁም ከውጪ የተለያዩ ተቋማት ጣልቃ ገብነት የጸዳና በገለልተኝነት ስራውን የሚከውን ተቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳቸውን ለምክክር ኮሚሽን ማቅረባቸውን የገለጹት መስፍን (ፕ/ር)÷ የትግራይ ክልል ሕዝብ ከፍተኛ የንግግር ፍላጎት ያለው፣ ስለሰላም ከማንም በላይ የሚረዳና ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ፍላጎት ለምክክሩ ስኬት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ የተወሰኑ አካላት አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ ማቅረባቸው ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው÷ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version