Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና ትጥቅ የፈቱ አባላት በተሃድሶ ሂደት እያለፉ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሱዳን የቆዩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና ትጥቅ የፈቱ አባላት በተሃድሶ ሂደት እያለፉ ይገኛሉ አለ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን።

በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል የተሃድሶ ሥልጠና የተከታተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ሂደቱን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ በወቅቱ እንዳሉት፤ የቀድሞ ታጣቂዎች የመረጡት የሰላም መንገድ ለሌሎች ትምህርት ይሆናል።

መንግሥት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የሰላም አማራጭን በመከተል ትጥቅ ፈትተው ለሚመጡ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ ሥራ ሰላምን ለማጽናትና የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት ኃይል እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች ከ85 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ በመፍታትና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።

የቀድሞ ህወሃትን በመደገፍ የተዋጉና በሱዳን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የቆዩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባለ የሚጠራ ቡድን አባላት ወደ ሀገራቸው ገብተው ለፌዴራል መንግሥት በግልጽ ያቀረቡት የዲሞቢላይዜሽን ጥያቄ ተቀባይነት ማገኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህም በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አማካኝነት በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል የተሃድሶ ሥልጠና የመስጠትና ሂደቱን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ መጀመሩን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሂደቱም ከ500 በላይ የሚሆኑ ትጥቅ የፈቱ አባላትን በማዕከሉ በመቀበል፣ የስነ ልቦና እና የስነምግባር እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳይ ስልጠናዎች እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል።

Exit mobile version