አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በአደራ የተሰጠውን ህጻን ታማሚ አካል ጉዳተኛ በማስመሰል ገንዘብ ሲያሰባስብ የተያዘው ግለሰብ በእስራት እንዲቀጣ ወሰነ።
የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት የልዩ ልዩ ወንጀሎች ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ሚኪያስ ንጉሴ የተባለው ግለሰብ ላይ፤ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3 እና 4 የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦበት ነበር።
በዚህም ተከሳሹ ከአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ለማሳደግ በአደራ የተሰጠውን የባለቤቱን የወንድም ልጅ የአራት ዓመት ህጻንን የጉበት ታማሚ እና አካል ጉዳተኛ በማስመሰል በጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን በሆለታ ከተማ ቡርቃ ሀርቡ በተባለ አካባቢ በዊልቸር ላይ አስቀምጦ በልመና ገንዘብ ሲሰበስብበት እንደነበር በክሱ ዝርዝር ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ ህጻኑን በገበያ ቦታ ላይ በልመና አሰማርቶ ገንዘብ ሲሰበስብ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ጥቆማ መስጠታቸውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውሎ በተደረገ ማጣራት ህጻኑ ጤነኛ መሆኑ መረጋገጡን በክሱ ላይ ተመላክቷል።
ተከሳሹም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ ክዶ በመከራከሩ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሹ “ምንም አይነት የመከላከያ ማስረጃ የለኝም” በማለቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሹ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን፤ ህጻኑ ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ታዝዟል።
በታሪክ አዱኛ

