Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ያላትን ተፈጥሯዊ መብት…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የውጭ ጫናዎችን በጽናትና ተግባራዊ ስኬቶች እያከሸፈች በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት ታረጋግጣለች አሉ የፖለቲካና ዓለም አቅፍ ግንኙነት ባለሙያ አሊ ሁሴን (ዶ/ር)።

ባለሙያው ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያ ለደኅንነቷና እድገቷ ባሕር በር ማግኘት እንዳለባትና ተዘግቶባት እንደማትኖር አስረድተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት የታየው የሕዝቡ አንድነት፣ ጥንካሬና ስልታዊ ዲፕሎማሲ ለባሕር በሩ መሳካት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ለዓመታት የሚሰነዘሩባትን ዛቻዎችና ሰው ሰራሽ መሰናክሎችን ችላ በማለፍ ግድቡን ለፍጻሜ ማብቃቷ አሁንም ለሚገጥሟት ጫናዎች ስልታዊ ምላሽ ለመስጠት ትልቅ የሥነ ልቦና ስንቅ እንደሚሆናት ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ ከጩኸት ይልቅ በዝምታ ወደ ተግባር የመግባት ልምድ ማዳበሯ የባሕር በር ጥያቄዋንና የቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጉዞዋን ለማሳካት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ልትቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።

ይህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተው÷ ዜጎቿም ዲጂታል አርበኞች በመሆን ጥያቄዋን ለዓለም ማስተጋባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውስጥ ጽናትና በጠንካራ ስራ የምታስመዘግባቸው ድሎች በቀጣናው ያላትን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅም ሆነ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ ሚና እንዳሚጫወት ገልጸዋል።

በቅድስት ዘውዱ

ከፖለቲካና ዓለም አቅፍ ግንኙነት ባለሙያ ጋር የተደረገውን ቆይታ ለመከታተል ማስንፈጠሪያውን ይጫኑ👇
https://www.youtube.com/watch?v=BaZnupmVmJo

Exit mobile version