አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ ቁልፍ መስመር የሆነው የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ወታደራዊ ፍጥጫ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የአሜሪካ ባሕር ሃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጥበቃ ለማድረግና ለማጀብ ዝግጁ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ÷ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የተከሰተው የነዳጅ ምርት ዋጋ መናር ለዋሺንግተን የማያሰጋና ጥሩ እድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ በማሻቀቡ አሜሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ብታገኝም ዋናው ትኩረቷ ግን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት መከላከልና ወታደራዊ አቅሟን ማዳከም ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አሜሪካ ትልቅ የነዳጅ አምራች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ ከስትራቴጂክ ክምችቷ ውስጥ ያለውን ነዳጅ ለገበያ እንደምታውል አመልክተዋል።
አዲሱ የኢራን መንፈሳዊ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በበኩላቸው÷ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የመዝጋቱን ሒደት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ የባሕር ላይ ፈንጂዎችን በመጥመድና በንግድ መርከቦች ላይ የሚሳኤል ጥቃት በመሰንዘር መስመሩን አደገኛ አድርጋው ሰንብታለች ነው ያሉት።
ኢራን በአሜሪካ እና እስራኤል ለሚፈጸምባት ጥቃትና እስካሁን ለደረሰባት ጉዳት አጸፋዊ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነች ማስገንዘባቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የነዳጅ ንግድ ቁልፍ መስመር የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ የሚቆይ ከሆነም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
በሶስና አለማየሁ

