አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ፍቼ ጫምባላላ’ ከነገ ጀምሮ በልዩ ልዩ ባህላዊ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል።
ፍቼ ጫምባላላ ለሀገራዊ መግባባት፣ ለአንድነትና ለሰላም ጉልህ አበርክቶ ያላቸውን እሴቶች አቅፎ የያዘ በዓል ነው፡፡
በዓሉ ከ11 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይደሳስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ያስቻሉትም የእርቅ፣ የሰላምና የአንድነት እሴቶቹ ናቸው፡፡
የበዓሉ ዝግጅት አካል የሆነው ‘ኡሱራ’ የተሰኘው የሲዳማ ብቁ አረጋዊያን (ጭሜየ) የሚይዙት የጾም ስርዓት ከበዓሉ ቀደም ብሎ ባሉ ቀናት የሚከናወን ሲሆን፥ ይህም ስላለፈው በደል ንስሃ የሚገባበትና መጪው ጊዜ የሰላም እንዲሆን የመማጸኛ ወቅት ነው፡፡
በኡሱራ ከሚከወኑ ስርዓቶች አንዱ የተጣሉ ሰዎችን ማስታረቅ ሲሆን፥ ይህም ሰዎች ተጣልተው ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገር የለባቸውም በሚል እሳቤ የሚፈጸም ነው፡፡
የሲዳማ ብሔር የሀገር ሽማግሌዎችና ባህል አዋቂዎች ይህ የእርቅ ስነስርዓት ‘አፊኒ’ የተሰኘው የሲዳማ የውይይት ባህል የሚገለጥበት ሁነት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እርቅ፣ ውይይትና ፍትህን አቅፎ የያዘው አፊኒ በዳይና ተበዳይ ሀሳባቸውን የሚናገሩበትና ለመደማመጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ዘመናትን የተሻገረ የሲዳማ ህዝብ መገለጫ ነው፡፡
የአፊኒ ስርዓት የመመካከር፣ የመደማመጥና የእርቅ እሴቶች እንደ ሀገራዊ ምክክር ላሉ የውይይትና የመፍትሄ መድረኮች በብዙ የሚፈይዱ ናቸው፡፡
‘ሰላም’ የፍቼ ጫምባላላ አስኳል መሆኑን የሚገልጹት የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች፥ ከእርቅ እሴትነቱ ባሻገር የሰላምና የአንድነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጭሜየ በመባል የሚታወቁት ሽማግሌዎች ከበዓሉ ቀደም ብሎ ኡሱራ የተሰኘውን ፆም በመግባት ለሀገር፥ ለህዝብና ለእንስሳት ጭምር ሰላም እንዲሰፍን ፈጣሪን ይማጸናሉ።
በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ተናፍቆ የሚጠበቀው ፍቼ ጫምባላላ የአብሮነትና የአንድነት በዓል እንደመሆኑ ወንድ ሴት፣ ህጻን አዛውንት፣ ሀብታም፣ ድሃ ሳይባል ሁሉም በጋራ የሚያከብረው ትልቅ በዓል ነው፡፡
የሲዳማ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ህዝቦች ጭምር በዓሉን በጋራ የሚያከብሩት ሲሆን፥ የጋራ እሴት በማዳበር የባህል ልውውጥ የሚደረግበት ትልቅ ሁነት ነው፡፡
በተጨማሪም ፍቼ ጫምባላላ ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋፅኦ በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ ካስቻሉት እሴቶች አንዱ ነው፡፡
በፍቼ ጫምባላላ ዛፍ አይቆረጥም፣ መሬት አይቆፈርም፥ አደን ስለማይታደን ሁሉም ተፈጥሮ ይከበራል፣ ያርፋል፣ ከብቶች አይታረዱም እንዲያውም በአዲስ የግጦሽ ሣር ይለቀቃሉ።
የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ‘ፍቼ ጫምባላላ’ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ በልዩ ልዩ ሁነቶች ከነገ ጀምሮ ይከበራል።
በኃይለማርያም ተገኝ

