Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ፍቼ ጫምባላላ የጎላ ፋይዳ አለው – ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወንድማማችነት መርህ ላይ በተመሰረተ ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደት ፍቼ ጫምባላላ የጎላ ፋይዳ ያበረክታል አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ለሚከበረው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጫምባላላ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሲዳማ አባቶች (አያንቶዎች) በባህላዊ የስነፈለክ እውቀትና ጥበባቸው የስነ ከዋክብትን ዑደትና የወቅቶችን እርዝማኔና ንባሬ በማጥናት ሽርፍራፊ ሰከንዶችን ጭምር ቀምረው ጊዜያትን የሚለኩበትን የቀን አቆጣጠር መፍጠራቸውን በመልዕክታቸው አውስተዋል፡፡
ፍቼ ጫምባላላ ለሀገራችን ኩራት፣ ለሲዳማ ህዝብ የጥበብ ጥግ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ ለዚህ ትውልድ ከደረሱ ቀደምት እውቀቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓሉ የሴቶችና ህፃናት መብት የሚከበርበት፣ ወንድና ሴት፣ ህጻን አዋቂ የሚል ልዩነት ሳይፈጠር ለተፈጥሮና ስነ ምህዳር፣ ለእንስሳት፣ ለደን፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲደረግ የሚያስገነዝቡ እሴቶችን አቅፎ የያዘ ነው ብለዋል፡፡
በእነዚህ እሴቶች የዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዘኛዎችን የሚያሟላ በመሆኑ ከ11 ዓመት በፊት በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡
ከአሮጌው ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ የሆነው ፍቼ ጫምባላላ ቂም፣ ቁርሾና በቀል ይዞ ወደ አዲሰ ዘመን መሻገር ስለማይፈቀድ የሲዳማ ህዝብ በሁሉቃ ስርዓት ይቅርታ የሚያወርድበት በዓል ነው።
የተጣላ የሚታረቅበት፣ በሰዎች መካከል መቻቻልና አብሮነት የሚጎለበትበትና የሲዳማ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያለውን ወንድማማችነት የሚያንፀባርቅበት በዓል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዓሉ የሲዳማ ህዝብ ባህላዊ የስነ ከዋክብት ጥናት ጥበብ ለዓለም ህዝብ የተዋወቀበት መሆኑን አውስተው፥ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
ለባህላዊ ጥበቦችና እውቀቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የጋራ አብሮነትን የሚያጠናክሩ እሴቶችን ለማፅናት እየተሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ፍቼ ጫምባላላ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በዓሉን በአንድነት፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
Exit mobile version