Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወቅታዊ መረጃን ከማሰራጨት ባለፈ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እያሰጠ የሚገኘው ጎንደር ፋና ኤፍ ኤም…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ፋና ኤፍ ኤም ለሕዝቡ አማራጭ መረጃን በወቅቱ ከማድረስ ባለፈ የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ እያደረገ ነው ፡፡

የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ሬዲዮ ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ዮሀንስ እንዳሉት÷ ጣቢያው በክልል ኤፍ ኤም ከተመሰረቱ የሬዲዮ ጣቢያዎች አንጋፋ ነው።

ጣቢያው ከ17 ዓመት በፊት መጋቢት 5 ቀን ነበር ሥርጭቱን በጎንደር ከተማ በውስን የሰው ሃይል የጀመረው።

ባለፉት ዓመታትም ጣቢያው የአካባቢውን ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና የተፈጥሮ ሀብት በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ነው።

ለአድማጭ የቀረቡ ይዘቶችን በዜናና ፕሮግራሞች በመቅረጽ ጣቢያው በቀደሙት ዓመታት የሕዝብና መንግሥት ልሳን በመሆን ማገልገሉን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ጣቢያው በጎንደር መመስረቱ ለአካባቢው ማሕበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ሬዲዮ ጣቢያው ለዘመኑ በቀረቡ አማራጮች መረጃዎችን ለአድማጮች በማድረስ ለሕዝብ ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ የጣቢያውን ምስረታ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ በፋና ሚዲያ ኮርፓሬሽን የጎንደር ቅርንጫፍ ሬዲዮ ጣቢያ መንግሥትና ሕዝብን በቀጥታ በማገናኘት የልማት ጥያቄ እንዲመለስ ትርጉም ያለው ሥራ አከናውኗል።

ሚዲያው በ17 ዓመታት ጉዞው በሰላም ግንባታ፣ የዞኑን የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ነው ያሉት ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ም/ ከንቲባ ደብሬ የኃላ በበኩላቸው ÷ ጎንደር ፋና ኤፍ ኤም የከተማው ሕዝብ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል

በከተማዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በመለየትና የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችን በመጠየቅ በአድማጩና መንግሥት መካከል መተማመን እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ጣቢያው የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ በማስቀጠል በሀገረመንግስት ግንባታና የሰላም ዕሴቶችን በማጉላት በትኩረት እንዲሰራ የሥራ ሃላፊዎቹ አስገንዝበዋል።

የጣቢያው አድማጮች በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት÷ ጎንደር ፋና በመዝናኛ እና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ተወዳጅ ርዕስ ጉዳዮችን እየዳሰሰ ነው።

በምክንያት መርጠን የምናደመጥው ጣቢያ ነው የሚሉት አድማጮች ÷ ተደራሽነቱን ይበልጥ እንዲያሰፋም ጠይቀዋል።

ጣቢያው በእስካሁን ሒደቱ በአድማጭነትና ተሳታፊነት፤ በተባባሪነትና በአጋርነት አብረውን ለሚሰሩ ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።

ጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተመሰረተበት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በምናለ አየነው

Exit mobile version