አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፍቼ ጫምባላላ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ሰላም የሚሰበክበት ታላቅ ኢትዮጵያዊ በዓል ነው አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር።
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፍቼ ጫምባላላ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።
አፈጉባዔ አገኘሁ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማን ቋንቋ ባህልና አኗኗርን ለዘመናት ጠብቆ የቆየና ለዓለምም ያስተላለፈ ድንቅ ስርዓት ነው ብለዋል።
በዓሉ አሮጌው ዘመን አብቅቶ አዲስ ዓመት የሚጀመርበት ብቻ ሳይሆን ቂም እና ቁርሾ ተወግዶ ዕርቅ የሚወርድበት እንዲሁም ሰላም የሚሰበክበት ታላቅ በዓል እንደሆነም አመልክተዋል።
ፍቼ ጫምባላላ አብሮነትን፣ ሰላምንና ይቅርታን እያስተማረ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ ሺህ ዓመታትን የተሻገረና በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የተመዘገበ ታላቅ የአደባባይ በዓል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዓሉ የሲዳማ ሕዝብ ቋንቋን፣ ባሕሉንና ታሪኩን የማበልጸግ እና የመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ያረጋገጠበት ከመሆኑ ባሻገር ማሕበራዊ አንድነቱንና ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር ሰንደቅ ሆኖ ሲያገለግለው መኖሩን አብራርተዋል።
ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ሕዝብ በራሱ ባሕላዊ ዕውቀት እና ሥርዓት ራሱን የሚያስተዳድርበት እና የሚያከብርበት የነጻነትና የአንድነት በዓል መሆኑን ገልጸው÷ ይህንን የመሰለ ውብና ድንቅ ባህል ጠብቆ በማቆቱ ኢትዮጵያ ታመሰግናለችም ነው ያሉት።
ይህ በዓል ከነታሪኩና ሥርዓቱ ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ወጣቱ ትውልድ ባልተገቡ የባዕዳን ባህሎች ሳይመረዝ የራሱን ድንቅ ባህል በማስተዋወቅና በመጠቀም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በጥላሁን ይልማ

