አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ ሊቫኖስ ቀበሌ 90 ሺህ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን በመጠቀም 20 ኩንታል ጤፍ የገዙት የገዙት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።
ሶስት ተጠርጣሪዎች የጤፍ ነጋዴ ከሆነ ግለሰብ 20 ኩንታል ጤፍ በመግዛት ብር ሲረካከቡ የጤፍ ነጋዴው ሀሰተኛ የብር ኖት እንደሆነ በመረዳት ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥቷል።
ፖሊስም ጥቆማውን ተቀብሎ ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፈንጅ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም ÷ 90 ሺህ 100 ሀሰተኛ የብር ኖት ፣ 13 ሺህ 7 መቶ ህጋዊ የብር ኖት ፣ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከ6 መሰል ጥይት እና ስድስት ተንቀሳቃሽ ስልክ እንደተገኘባቸው ከክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የወረዳው የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ፀጋዬ ጋሹ እንደገለፁት በመጭው አዲስ አመት ወቅት ህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ግብይቶችን ሲያከናውን ለእንደዚህ አይነቱ የወንጀል ድርጊት ሰለባ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥምም ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን የመከላከል ተግባሩን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

