Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የብዝኃ ሃይማኖት ሀገር ናት – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ረገድ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ ሚና ማበርከቷን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያኗ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ ታሪኮችንና ትውፊቶችን ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር፣ ትውልድን በማነጽ፣ ግብረገብነትንና ሰብዓዊ ርኅራኄን በማስተማር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር እንዲሁም በልማት ተሳትፎ የጎላ ድርሻ ስትወጣ ቆይታለችም ነው ያሉት።

በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ቤተክርስቲያኗ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አንስተን ተቀያይተናል ብለዋል።

በውይይቱም ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለሰላም፣ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም መግባባት ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።

ውይይቱ የተነሱ አንዳንድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ እንደነበር ገልጸው÷ ይህም በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያና የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑን አብራርተዋል።

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አመራሮች ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጡት ገንቢ ሐሳብ ምስጋና አቅርበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትናንትናው ዕለት በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች እና ምእመናን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

Exit mobile version